1. የማኅበራዊ ፕሮግራም ዓላማ፡– 

ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ አካታች ማኅበራዊ ልማት

ሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት መነሻዋ ዝቅተኛ ደረጃ በመሆኑ ሁለንተናዊ ማኅበራዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ጉዳይ የፓርቲያችን ማኅበራዊ ፕሮግራም አንድ ዋና ትኩረት ይሆናል። በመሆኑም የማኅበራዊ ልማት ሥራዎቻችን የዕድገትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መንትያ ግቦችን የማሳካት ጉዳይ ይሆናል። የማኅበራዊ ልማት ሥራዎቻችን ከችሮታና ከነባሩ የማኅበራዊ ደኅንነት ትኩረት ወጥቶ ችግሩን ከመብት አንፃር የሚመለከተው ይሆናል። ማኅበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተደራሽነትና አካታችነትን ባለው መልኩ የማኅበረሰብን ጤና፣ ደኅንነት እና ምቾት የሚያስጠብቅ መሆን ይኖርበታል። የማኅበራዊ ፕሮግራማችን ዜጎችን የሚስተሣሥር፣ ከችግርና ከመከራ የሚታደጋቸው፣ የሀገርን አለኝታነት የሚያሠርጽ እና በሀገራችን አዎንታዊ ሰላምን የሚያረጋግጥ ይሆናል። የማኅበራዊ ልማት ፕሮግራማችን ኅብረ ሀገራዊ ማንነትን መሠረት ያደረገ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብት እንዲሆን ዒላማ አድርጎ መንቀሳቀስ የፓርቲያችን የማኅበራዊ ፕሮግራም ዓላማ መገለጫ ይሆናል። ይህንንም እውን ለማድረግ በማኅበራዊ ልማት ዘርፍ የአርሶ አደሩን እና አርብቶ አደሩን፣ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የከተማ ነዋሪ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፓርቲያችን ይሠራል።

 1. የማኅበራዊ ፕሮግራም ግቦች
  1. ፍትሐዊነት፣ ጥራት፣ አካታችነት እና አግባብነት ያለው የትምህርት ሥርዓት ማረጋገጥ፡
   1. በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የትምህርት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ ፓርቲያችን ይታገላል። በዚህም መሠረት የቅደመ መደበኛ ትምህርት በሀገራችን ሙሉ ለሙሉ እንዲዳረስ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ይደረጋል፡፡
   2. ትምህርትን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽና ፍትሐዊ በማድረግ በኩል የአንደኛ ደረጃና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት /ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል/ ሁሉም ዜጐች ትምህርት እንዲያገኙ ፓርቲያችን ይታገላል፡፡ ለዚህም ሀገራዊ ስታንደርዳቸውን የጠበቁና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ትምህርት ቤቶች ሕዝቡን በማሳተፍ እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡ በሌላ በኩል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ኢኮኖሚው በሚፈልገው መልኩ በሦስት ዘርፎች ማለትም የአጠቃላይ ትምህርት፣ መሠረታዊ የቴክኒክና ሞያ እንዲሁም በልዩ ተሰጥዖ ትምህርት ተደራጅቶ እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡
   3. አሁን ያለውን የሀገራችን ዕድገት በጐልማሳው ትከሻ ላይ የወደቀ በመሆኑ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጐልማሶች ትምህርት ጐልማሳው የራሱን ሕይወት እንዲቀይር ብሎም በሀገሪቱ ዕድገት ላይ ትርጉም ያለው አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ለማድረግ ኘሮግራሙ ተቃኝቶ ተግባራዊ እንዲሆን ፓርቲያችን ይታገላል፡፡
   4. ፓርቲያችን በዋናነት የትምህርት ተደራሽነትን አረጋግጦ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች የትምህርት ጥራትን ማሳደግ የትምህርት ፕሮግራሙ ዋነኛ ዓላማ አደርጎ ይታገላል። የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ክሂሎትን መሠረት ያደረገ፣ የሀገር በቀል ዕውቀት ያካተት፣ ዜጐች ችግር ፈቺና ተመራማሪ ሆነው እንዲገነቡና ለሀገራቸው ብልጽግና የሚተጉ እንዲሆኑ፤ መምህራን በተሻለ ችሎታና ሥነ ምግባር የታነፁ ሆነው ትውልድን በዕውቀት፣ በክሂሎት እና በመልካም ሥነ ምግባር የሚቀርፁ፣ እንዲሁም የሚገባቸውን ሞያዊ ክብርና ጥቅም እንዲያገኙ ሀገራዊ የመምህራን ልማት ኘሮግራም በማሻሻል ፓርቲያችን ይሠራል።
   5. የቴክኒክና ሞያ ትምህርትና ሥልጠና የውጤት ተኮር ሥርዓት መሠረት በማድረግ እስካሁን በሀገራችን እየተተገበረ ያለ ቢሆንም በተለያዩ ያተገባበር ችግሮች ምክንያት የተፈለገውን ውጤት አላመጣም፡፡ በአተገባበር የታዩ ችግሮችንና ተግዳሮቶችን በመቅረፍ የኢንዱስትሪውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ለመሙላት በሚያስችል መልኩ እንዲደራጅ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቴክኒክና ሞያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት፣ ዐቅማቸው እንዲጎለብት ተደርጎ ለኢንዱስትሪው የጀርባ አጥንት የሆነ ብቃት ያለው የሰው ኃይል እንዲያመርቱ ከማድረግ ባሻገር ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ያደርጋል።
   6. የሀገራችን ከፍተኛ ትምህርት ከኢንዱስትሪው የሰው ኃይልና የምርምር ፍላጎት ጋር ትሥሥርና አግባብነት ያለው እንዲሆን ፓርቲያችን ይሠራል። የከፍተኛ ትምህርት ቅበላ ሥርዓቱ የተማሪዎችን ፍላጎትና ዝግጁነት ግምት ውስጥ በማስገባት የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎትና ዐቅምን ባገናዘበ መልኩ እንዲቀረፅ ያደርጋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተለየ ተልዕኮ ላይ አተኩረው፤ ከማስተማር ሥራ ባሻገር ጥናትና ምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ላይ በማተኮር ለኅብረተሰቡ ችግር መፍትሔ የሚሰጡ ሆነው ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዕውቀትና የጥበብ መናኸሪያዎች፣ ብዝኃነትን የሚያጎለብቱና እርስ በእርስ መቀራረብን የሚፈጥሩ የዓለም አቀፋዊ ዕሴቶችና አስተሳሰቦች ማዕከላት እንዲሆኑ ፓርቲያችን አበክሮ ይሠራል።
   7. ፓርቲያችን ሁሉም የትምህርት ተቋማት የአካዳሚ ነጻነትን ከሚያቀጭጩ ፖለቲካዊም ሆነ ከአስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነቶች ነጻ እንዲሆኑ በማድረግ፣ በዕለት ተዕለት የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የኅብረተሰብ አገልግሎት ሥራ ሁሉም ዕይታዎች በእኩል መድረክ አግኝተው በነጻነት የሚንሸራሸሩባቸው እንዲሆኑ ይሠራል።
   8. የሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርት አብሮነትን በማሳደግና ግብረ ገባዊ ዕሴቶችን በማስፋትና በማስረፅ በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ ሀገር ወዳድ ትውልድ በማፍራት ረገድ የሚጫወተው ሚና እጅግ የላቀ እንደሆነ ፓርቲያችን ይረዳል። ስለዚህ የተማሪዎችን ባህሪያት መልካም ለማድረግ የግብረ ገብ ትምህርት እስከ 6ኛ ክፍል ራሱን ችሎ እንዲሁም ከ7ኛ ክፍል በኋላ በሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርት ተካቶ ሀገራዊ አብሮነትን እና ኅብረ ሀገራዊነትን የሚያጠናክር፣ የሀገር ፍቅርን የሚያፀና እና ግብረ ገብነትን የተላበሰ ትውልድ መፍጠሪያ ተደርጎ እንዲቀረፅ ያደርጋል።
   9. ፓርቲያችን በአንደኛ ደረጃና በመካከለኛ ደረጃ የትምህርት ቋንቋ ብዝኃ ልሳን እንዲሆን የሚያደርግ ሲሆን ብዝኃ ልሳንነቱ የምንገነባውን ኅብረ ሀገራዊ አንድነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከክልሎች ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚጣጣም መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን ያደርጋል።
  2. መከላከልን መሠረት ያደረገ የጤና ሥርዓት መዘርጋት
   1. ፓርቲያችን በዋናነት በሽታን በመከላከል ላይ የተመሠረተ የጤና ጥበቃ ሥርዓት እንዲዘረጋ ያደርጋል። በተጨማሪም አክሞ የማዳን ዐቅምን በዘላቂነት ለማሳደግ የሰው ኃይል፣ ሥርዓትና ቴክኖሎጂ ዐቅም ግንባታ ላይ ፓርቲያችን ቅድሚያ ይሰጣል።
   2. ፓርቲያችን ለእናቶችና ሕጻናት ጤና ክብካቤ ልዩ ትኩረት በመስጠት ይሠራል የሴቶች ጤና የሥነ ተዋልዶ ጤና ችግር ለመቅረፍ፣ ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች እንዲወገዱ እና አጠቃላይ የሴቶችን ጤና ለመጠበቅ ከቅድመ ወሊድ እስከ ድኅረ ወሊድ ድረስ በአቅራቢያቸው በጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲያገኙ ፓርቲያችን ይታገላል። ሀገራችን በጤና ዘርፍ ወደ ኋላ የቀረችባቸዉን ዘርፎች አንዱ የሆነው የጨቅላ ሕፃናት ጤና እንክብካቤ ትኩረት እንዲሰጠው ይሠራል።
   3. በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ያሉ ዜጎችን ታሳቢ ያደረገ የነጻ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጥበት አሠራር እንዲዘረጋ ያደረጋል። ከዚህም በተጨማሪ የጤና መድኅን ሽፋን በመላ ሀገራችን እንዲዳረስ አሠራርን በማዘመን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደረጃውን የጠበቀ የጤና መድኅን ሽፋን ተጠቃሚ እንዲሆን ያደረጋል።
   4. ፓርቲያችን ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና የሥነ ሕዝብ ፓሊሲ መሠረት ነው ብሎ ያምናል። ፓርቲያችን የሕዝብ ቁጥሩ ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን ጋር ተመጣጥኖ እንዲሄድ እንዲሁም ጤናማ የሆነ ኅብረተሰብ ለመፍጠር የሚያስችል በፍላጎት ላይ የተመሠረተ የቤተሰብ ምጣኔ ፕሮግራሞች እንዲዘረጉ ያደርጋል።
   5. የሕክምና ባለሞያዎች ፍልሰትን በተለይም ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ የባለሞያዎችን ፍልሰት ለመቀነስ በገጠር የሚሠሩ ባለሞያዎችን ልዩ ጥቅምን ይሰጣል።
   6. የሕክምና ቁሳቁስ እጥረትን ለመቀነስ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል። የሕክምና ቁሳቁሶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ የሚደረግበት ዐቅም እንዲፈጠር ፓርቲያችን ይሠራል።
   7. የባህል ሕክምና እንዲዘምን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከዘመናዊ ሕክምና ጋር እንዲደጋገፍና በጥናትና ምርምር እንዲልቅ ያደረጋል።
 1. የሀገራችንን ዐቅም ያገናዘበ የማኅበራዊ ጥበቃ ሥርዓት መዘርጋት
  1. የማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓታችን ሕዝባችንን ከአስከፊ ችግርና ከጉስቁልና ኑሮ በመጠበቅ ጤናማ ማኅበረሰባዊ መስተጋብር እንዲኖር ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ ያደረጋል። ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ዐቅም ያገናዘበ፣ አካታችና ጥራታቸውን የጠበቁ የማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓቶችን ፓርቲያችን እንዲዘረጋ ይደረጋል።
  2. የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ መብት፣ ክብርና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በሙሉ ቁርጠኝነት ይሠራል። የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በተሻለ ሁኔታ በመምራት አካል ጉዳተኞች እንደ ማንኛውም ዜጋ በሀገራቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሠራል።
  3. ፓርቲያችን አሠሪና ሠራተኛ በሥራ ቦታ ጤናማ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው፣ የሥራ ቦታዎች ምቹና ጤናማ እንዲሆኑ እና የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ይሠራል። ሠራተኛው ከኢንዱስትሪው ምርታማነት ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆንና በነጻነት ተደራጅቶ የመንቀሳቀስ መብቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲከበርለት እና አሠሪውም ተገቢ ጥበቃ እንዲያገኝ ይደረጋል።
 1. የሴቶችንና ወጣቶች የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማጎልበት
  1. ሴቶችና ወጣቶች በሚደርስባቸው ሁለንተናዊ ጭቆና ምክንያት የኢኮኖሚያዊና የፖለቲካ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው አሁንም በሚፈለገው ልክ አለመሆኑ ፓርቲያችን ይረዳል። በመሆኑም  የሴቶችና ወጣቶች ፍትሐዊ የፖለቲካ ውክልናና ተሳትፎ እንዲሁም ዘላቂ የሥራ ዕድል፤ የብድር አቅርቦት፣ የመሬት ባለቤትነት፣ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚነት እና ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ እንዲያገኙ ፓርቲያችን ይታገላል፡፡ 
  2. ፓርቲያችን አጠቃላይ ኢኮኖሚና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎቻችን ወጣቱን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ ይሠራል። ወጣቶች በተማሩት የትምህርት ደረጃ፣ ባላቸው ዕውቀት፣ እንዲሁም በጥናት አዋጪ በሆኑ ዘርፎች ላይ እንዲሠማሩና ውጤታማ እንዲሆኑ ሰፋፊ የሥራ ዕድል አማራጮችና ዕድሎች እንዲፈጠሩ ፓርቲያችን ይሠራል። የወጣቶችን የስፖርት ማዘውተሪያዎችና የመዝናኛ ሥፍራዎችን በጥራትና በብዛት በማሳደግ ወጣቶች ንቁና ገብረ ገብነትን የተላበሱ እንዲሆኑ እንዲሁም ከሱስና ከጥፋት የራቁ እንዲሆኑ ፓርቲያችን ይሠራል።
  3. ፓርቲያችን የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት በሕግ እና በተቋም ታግዞ ዜጎች ለተገቢ አገልግሎት ተገቢ ክፍያ እንዲያገኙ ክትትል እና ድርድር በማድረግ የዜጎች ደኅንነት እና ክብር እንዲጠበቅ ይታገላል።  
 1. ብዝኃነታችንን ማዕከል ያደረግ የባህልና ቅርስ ልማት
  1. ኅብረ ሀገራዊ ሀገር የመፍጠር ትልምን እውን ለማድረግ ይረዳ ዘንድ የሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋዎች እንዲያድጉና እንዲጎለብቱ የሕግ፣ ተቋማዊ እና አስተዳደራዊ ሥራዎች ተግባራዊ ያደርጋል። የኢትዮጵያን ብዝኃነትን በሚገልጽ መልኩ ተጨማሪ የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋዎች ሥራ ላይ እንዲውሉ ፓርቲያችን ይታገላል።
  2. ፓርቲያችን የኢትዮጵያዊ የጋራ ዕሴቶችና ባህሎች እንዲጎለብቱ፣ ታሪካዊ ቅርሶቻችን፣ የሚዳሰሱም ሆነ የማይዳሰሱ ባህላዊና ትውፊታዊ ቅርሶቻችን ተገቢው ክብርና ትኩረት ተሰጥቷቸው፣ ከአደጋ ተጠብቀው ለሀገር ግንባታ መሣሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ እና ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ በትኩረት ይሠራል። ፓርቲያችን የቀደሙ ቅርሶችን ከመጠበቅ ባሻገር ዘመን ተሻጋሪ የትውልድ አሻራና ቅርስ ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ አበክሮ ይሠራል፡፡
  3. ፓርቲያችን ስፖርት ሀገራዊ ክብርን እና ሀገራዊ መቀራረብን የሚያረጋግጥ የብልጽግና አንድ አካል እንደሆነ ይረዳል፡፡ ‹ስፓርት ለሁሉም‹ በሚል መርሕ ሀገራዊ አንድነትንና የሕዝቦችን ወንድማማችነት ለማጠናከር ስፖርት ተቋማዊና ሕዝባዊ እንዲሆን ይሠራል።
  4. ኪነ ጥበብ በዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቱ ጎልብቶ የሀገራችን ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ተጽዕኖ የመፍጠሪያ ኃይል እንዲሆን እንዲሁም ኪነ ጥበብ ለሕዝቦች መተዋወቅ፣ መቀራረብ፣ መግባባትና ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ መቆም ጠቃሚ እንደሆነ ፓርቲያችን ይገነዘባል፡፡ በመሆኑም ኪነ ጥበብ የማኅበረሰቡን ጠቃሚ ዕሴቶች ለማጎልበት ተገቢውን ሚና እንዲወጣ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችኪነ ጥበባዊ ሀብት በትምህርትና ሥልጠና እንዲታገዝ፣ የኪነ ጥበብ ተቋማትና ማዕከላት ተሰፋፍተው ለሀገር ብልጽግና እንዲውሉ ይታገላል፡፡