ከዚህ በታች የተመለከቱትን መመዘኛዎች የሚያሟላ   ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ  የፓርቲው አባል መሆን     ይችላል።
 1. የፓርቲውን ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ተቀብሎ በጽናት ተግባራዊ ለማድረግ ፍቃደኛ የሆነ፣
 2. መልካም ስነ ምግባር ያለውና በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያለው፣
 3. በህብረ ብሄራዊነት እና በሀገራዊ አንድነት ላይ ፅኑ አቋም ያለውና ዋልታ ረገጥ አመለካከትና ተግባሮችን በፅናት የሚታገል፣
 4.  ዜጎችንና ህዝቦችን በእኩልነት የሚያገለግል፣ የህዝብ ጥቅምን የሚያስቀድም፣ ከሙስናና ብልሹ አሰራሮች ራሱን ያራቀና ሌሎችንም የሚታገል፣
 5.  የፓርቲውን ዕሴቶችና ዓላማዎችን ተቀብሎ የተሰጠውን ሃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ የሆነ፤
 6.  በፓርቲው መመሪያ መሠረት ወርሃዊ የገንዘብ መዋጮ ለመክፈል ፈቃደኛ የሆነ፤
 7.  ዕድሜው አስራ ስምንት ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆነ፣
 8. የሌላ ፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ፣
 9.  የፖለቲካ ድርጅት አባል የመሆን መብቱ በሕግ ያልተገፈፈ፤
 10.  በዚህ ደንብ በተወሰነው መሠረት የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ የፓርቲው አባል መሆን ይችላል።

 ለአባልነት የሚቀርብ  ጥያቄ

 1.  አንድ የፓርቲው አባል ለመሆን የወሰነ ዜጋ በአካባቢው ለሚገኘው የፓርቲው ጽህፈት ቤት በጽሁፍ ማመልከት ይኖርበታል፤
 2.  ከላይ በንዑስ አንቀፅ (1) የተቀመጠው እንደተጠበቀ ሆኖ በየደረጃው የሚገኝ የፓርቲው መዋቅር ለፓርቲው ፕሮግራምና መተደደሪያ ደንብ ታማኝና ለተግባራዊነቱም ይታገላል ብሎ ያመነበትን ግለሰብ ለፓርቲው አባልነት ሊመለምለው ይችላል፤
 3.  በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (1) እና (2) መሰረት መሥፈርቱን አሟልቶ የተመለመለ ግለሰብ ለስድስት ወራት በሙከራ አባልነት ይቆያል፤
 4.  የፓርቲው ጽ/ቤት የእጩ አባሉን አፈጻጸም አይቶ ሙሉ አባል የማድረግ ወይም ተጨማሪ ከሶስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ የእጩነት ጊዜውን ማራዘም ይችላል፣
 5. የእጩ አባልነት ቆይታ ከአንድ ጊዜ በላይ አይራዘምም፣
 6.  እጩ አባሉ በሙከራ ጊዜ ቆይታው ፓርቲው የሚሰጠውን ተልዕኮ ይፈጽማል፣
 7. የአባላት ምልመላ፣ ግንባታ፣ ስምሪት፣ ምደባ፣ ምዘናና ስንብት ዝርዝር መመሪያ በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ይወጣል።

የአባል መብት

1) ማንኛውም የፓርቲ ሙሉ አባል የሚከተሉት መብቶች ይኖሩታል፣

ሀ) በፓርቲው አካላት ምርጫዎች የመምረጥና የመመረጥ፣

ለ) በፓርቲው ጉባኤዎች የመሳተፍ፣ በውይይት የመካፈልና በድምጽ በሚወሰኑ ጉዳዮች ላይ ድምጽ የመስጠት፣ በማንኛውም ጉዳይ ላይ በህጋዊ መድረኮች ሃሳቡን በጽሁፍም ሆነ በቃል የማቅረብ፣

ሐ) በማንኛውም የፓርቲ አካል ወይም አባል ላይ በመረጃ የተደገፈ ሂስ የማቅረብ፣

መ) በየትኛውም የፓርቲ ውሳኔ ቅር ከተሰኘ ቅሬታውን በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት በየደረጃው ለሚመለከተው አካል የማቅረብ፤

ሠ) ስለራሱ፣ ስለአካሉ፣ ስለፓርቲው ማወቅ የሚገባውን ነገር እስከ ፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የመጠየቅና መልስ የማግኘት፣

ረ) የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ፣ ፕሮግራም፣ አቋሞችና ውሳኔዎች ለሌሎች የማሳወቅ፣ የማስተዋወቅ፣ የማስረፅና በተጨባጭ እንዲተገበር የማድረግ እና

ሰ) በየትኛውም ጊዜ በጽሁፍ አመልክቶ እና በእጆቹ የሚገኙ የፓርቲው ንብረቶች እና ሃላፊነት በአግባቡ አስረክቦ መልቀቅ ይችላል።

2) ማንኛውም ዕጩ አባል በየደረጃው ለፓርቲው አካላት የመምረጥና የመመረጥ እንዲሁም ድምጽ የመስጠት መብት የለውም፤ የሌሎች የአባልነት መብቶች ግን ተጠቃሚ ሲሆን፣ የግዴታዎችም ተገዥ ይሆናል።

የአባል ግዴታ

ማንኛውም የፓርቲ አባል የሚከተሉት ግዴታዎች ይኖሩበታል፤

1) በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ የፓርቲውን ፕሮግራም፣ መመሥረቻ ጽሁፍ፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ መመሪያዎች፣ ውሳኔዎችና ዕቅዶችን የማወቅ፣ የመቀበል፣ የማክበር፣ የመገዛት እና ለተግባራዊነታቸው በግንባር ቀደምትነት የመታገል፣

2) በሚገኝበት የሥራ መስክና የኃፊነት ደረጃ የፓርቲውን አንድነት፣ ጥራትና ጥንካሬ፣ የፓርቲውን የፖለቲካ እሳቤዎች ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ሙሉ ተሳትፎ የማድረግ፣

3) የፓርቲውን መርሆዎች፣ ዕሴቶችና የአባላት የሥነ ምግባር ሕጎችን ማክበር እና የፓርቲውን፣ የህዝብና የሀገርን ደህንነትና ሉዓላዊነት የመጠበቅ፣

4) የአገሪቱን ሕጎችና ልዩ ልዩ መንግስታዊ ውሳኔዎች ማክበር፣

5) በሀገራዊና አካባቢያዊ ምርጫ ወቅት የምርጫ ካርድ የማውጣት፣

6) የፓርቲውን አንድነት፣ ጥራትና ጥንካሬ የሚጎዱ ማናቸውንም ዝንባሌና ድርጊቶችን የማጋለጥና የመታገል፣

7) በፓርቲው ውስጥ በግለሰቦች ወይም ቡድኖች የተያዙ ተናጠል አቋሞችን የፓርቲው በማስመሰል በማናቸውም መልኩ በሚዲያ ከማሰራጨት የመቆጠብ፣

8) በአባላት መካከል የሚኖረውን መልካም ግንኙነት ከሚያጎድፉ ድርጊቶች የመታቀብ፣

9) በፓርቲው ውሳኔ መሠረት የአባልነት መዋጮ የመክፈል፤

10) የፓርቲው ንብረት በአግባቡ የመጠቀም፣

11) ከሙስና የፀዳ፣ ሙስናንና አድሏዊ አሰራርን የመታገልና የማጋለጥ ግዴታ እና

12) ከአንድ አካባቢ ወይም የስራ ቦታ ወደሌላ አካባቢ ወይም የስራ ቦታ በቋሚነት ለቅቆ ሲሄድ የለቀቀበትን እና የደረሰበትን የፓርቲ መዋቅር ማሳወቅ አለበት።