ከ5ኛው መደበኛ ጉባኤ ጀምሮ ሲነሳ የቆየው የኢህአዴግ የውህደት ጉዳይ በሀዋሳው የኢህአዴግ 11ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ዘግይቷል በሚል ተገምግሞ ወደ ፈጣን ተግባር እንዲገባ በጉባኤው ተሳታፊ ተወሰነ፡፡ በመሆኑም የውህደቱን ስራ በምን መልኩ መከናወን እንዳለበት ኃላፊነት የወሰደው የኢህአዴግ ምክር ቤት ማከናወን የነበረበትን ቀሪ ተግባራት አከናውኖ ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቀረበ፡፡ ህዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም የኢሕአዴግ ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ ተሰብስቦ ውህደቱን በ27 አብላጫና በ6 የተቃውሞ ድምፅ አጸደቀ፡፡ህዳር 7ቀንም ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በውህድ ፓርቲው ረቂቅ ፕሮግራም ላይ ተወያይቶ ረቂቁን ለኢህአዴግ ም/ቤት መራ፡፡ ህዳር 9ቀን የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ “ብልፅግና ፓርቲ” የሚለው ስያሜ ለኢህአዴግ ምክር ቤት እንዲቀርብ ከስምምነት ላይ ደረሰ፡፡ ህዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ምክር ቤት (ከህወሓት ውጭ) ውሕደቱን በሙሉ ድምፅ አጸደቀ፡፡ ህዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም. የአዲሱን ፓርቲ የወደፊት አቅጣጫ ያመለከተ መግለጫ ወጣ፡፡
ከእዚህ መግለጫ በኋላ እህትና አጋር ድርጅቶች (ከህወሓት ውጭ) ተራ በተራ የብልጽግና ፓርቲን መዋሀዳቸውን ይፋ አደረጉ፡፡ ህዳር 14 ቀን የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ብልፅግና ፓርቲን ለመቀላቀል ወሰነ፡፡ ህዳር 15 ቀን የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋ.ህ.አ.ዴ.ን) ከብልፅግና ፓርቲ ጋር የተጀመረውን ውህደት በመደገፍ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ፡፡ ህዳር 16 ቀን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ቤጉህዴፓ እና የሶዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ ወሰኑ፡፡ህዳር 17 ቀን አዴፓ እና ኦዲፒ ባካሄዱት አስቸኳይ ጉባዔ ብልፅግናን ለመቀላቀል በሙሉ ድምፅ መወሰናቸው ተነገረ፡፡ የሃረሪ ብሄራዊ ሊግ (ሃብሊ) በ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔው ብልፅግናን መቀላቀሉ በይፋ አስታወቀ፡፡ ህዳር 18 ቀን ደኢህዴን ብልፅግናን ለመቀላቀል ወሰነ፡፡ በእዚሁ ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) ውህደቱ ህግና ስርዓትን ጠብቆ መፈፀሙን አስታወቁ ፡፡
ህዳር 20 ቀን ውህድ ፓርቲውን የተቀላቀሉ ፓርቲዎች ፅ/ቤት ኃላፊዎች በተገኙበት የብልፅግና ፓርቲ የመጀመሪያ ስብሰባ ተካሄደ፡፡ህዳር 21 ቀን የብልፅግና ፓርቲን የተቀላቀሉ ድርጅቶች ይፋዊ የስምምነት የፊርማ ሥነ-ሥርዓት በአዲስ አበባ አካሄዱ (ብልጽግና ፓርቲ በይፋ ተመሰረተ)፡፡ ህዳር 24 ቀን ብልጽግና ፓርቲ ህጋዊ እውቅና እንዲሰጠው ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡
የፓርቲውን የስራ ቋንቋ በተመለከተም አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሱማሊኛ፣ ትግርኛ እና አፋርኛ የተመረጡ ሲሆን፣ ፓርቲው በአገሪቱ የሚገኙ ቋንቋዎች በሙሉ እውቅና እንዲያገኙም አድርጓል።