የብልጽግና ፓርቲ ጥቅል ዓላማ ” የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ“
የፓርቲያችን ጥቅል ዓላማ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው። ብልጽግና ስንል ፈርጀ ብዙ ትርጓሜን አዝሎ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ገጽታ ያለው ነው። የኢኮኖሚ ብልጽግና፣ የሕዝቦች መሠረታዊ ፍላጎቶች በተገቢና በዘላቂነት ለማሟላት የሚያስችል ፈጣን እና ሁለንተናዊ ዕድገትን በማስመዝገብ፣ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ያለው ኢኮኖሚ በመገንባት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና የሕዝቦችን ድኅነትና ኋላ ቀርነትን ለመቅረፍ መቻልን ያካተተ ነው። የፖለቲካ ብልጽግና ስንል ለዴሞክራሲ ባህል ማበብ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን በመገንባት፣ የሕዝቦች ነጻነትና እኩልነት ተረጋግጦ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸው የሚኖሩባት፣ ኅብረ ሀገራዊ አንድነቷ የተረጋገጠ፣ ፌዴራላዊት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ጽኑ መሠረት ላይ ማቆም ነው። ማኅበራዊ ብልጽግና መልካም ሀገራዊ ወጎችን፣ ዕሴቶችን እና ባህሎችን በማዳበር በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ማፍራት፣ በአካልና በአእምሮው የዳበረ ጤናማ ዜጋ መፍጠር፣ ከአስከፊ ማኅበራዊ ችግር የተጠበቀ ኅብረተሰብ መገንባት እና በሕዝቦች መካከል አዎንታዊ ሰላም በመፍጠር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ማለት ነው።