1. የኢኮኖሚ ፕሮግራም ዓላማ፡

                          ልማትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አካታች የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት

የብልጽግና ፓርቲ የሰው ኃይል ካፒታልን፣ ሸቀጥና አገልግሎት ያለ ገደብ በሀገራችን ከቦታ ቦታ በሰላምና በነጻነት ለመዘዋወር የሚያስችለውን ሁኔታ በማረጋገጥ፣ ሀገራዊ ትሥሥርን የሚያረጋግጡ የመሠረተ ልማት ግንባታ በማካሄድ እና አስፈላጊው ለሚሆኑበት ጉዳዮች ሀገራዊ ስታንዳርድ በማውጣት ለኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ግንባታ ይሠራልⵆ

የብልጽግና ፓርቲ በኢኮኖሚ ፕሮግራሙ የሕዝባችን ሰፊ ክፍል የሆነውን አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ ወጣት፣ ሴቶች እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የከተማ ነዋሪዎች ማዕከል ያደረገ አካታች የኢኮኖሚ ሥርዓት በመገንባት የሕዝባችንን የጋራ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ዓላማ ይኖረዋል። ፓርቲያችን በሀገራችን ምርታማነትን እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግሥት ወሳኝ ዐቅምና መሣሪያ ነው ብሎ ያምናል። በመሆኑም የመንግሥት በኢኮኖሚው ሥርዓት ውስጥ ያለው ተሳትፎ የገበያ መርሕን በመከተል ስትራቴጂካዊ በሆነ ሁኔታ ሀብት የሚፈጥር፣ በተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ማሕቀፍ ውስጥ የግሉን ዘርፍና ሌሎች የኢኮኖሚ ተዋናዮችን ተሳትፎ በማጎልበት ምርታማነትን በላቀ ደረጃና ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚያሳድግ እንዲሆን ያደርጋል። በዚህም መሠረት ፓርቲያችን ጥራት ያለውና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት እንዲሁም ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋገጥ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት ሀገራችንን ወደ ብልጽግና ጎዳና ለማሸጋገር ያልማል።

2. የኢኮኖሚ ፕሮግራም ግቦች

2.1. የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ መዋቅር መገንባT

 1. በአንድ ክፍለ ኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚ መዋቅር ዘላቂ ዕድገትንም ሆነ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እንደማያረጋግጥ ፓርቲያችን ያምናል። ስለሆነም ሀገራችን አንጻራዊ ዕምቅ ዐቅሞችን ታሳቢ በማድርግ ከግብርና በተጨማሪ የኢንዱስትሪ እና ተዛማጅ የአገልግሎት ዘርፎችን በማሳደግ ኢኮኖሚያችን በብዝኃ ዘርፍ የተዋቀረና ዘላቂ ዕድገት ያለው እንዲሆን ይሠራል። ይህን ለማሳካት ፓርቲያችን ሀገራችን ዕምቅ ጸጋ የታደለችባቸው ክፍለ ኢኮኖሚዎችን በሙሉ ዐቅም አሟጦ ወደ ልማት የማስገባት የኢኮኖሚ አቅጣጫን ይከተላል።
 2. ፓርቲያችን ሀገራችን ለግብርና ዘርፍ ያላትን የሥነ ምኅዳር ተስማሚነት፣ የመሬት እና ሰፊ የሰው ሀብት በሙሉ ዐቅም ሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ ልማትን ለማምጣት፣ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፣ የወጭ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ እና የግቢ ምግብ ነክ ሸቀጦችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት በትጋት ይሠራል። ይህም እንዲሆን ለማድረግ የግብርና ዘርፉ በግብዐትና ቴክኖሎጂ አቅርቦት እንዲሁም አመራረትና የገበያ ትሥሥር መሠረት ያደረገ ግብርናን የማዘመን ሥራ ይሠራል። ግብርናን በማዘመን ረገድ አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች በቂና የተሟላ ግብዐት እንዲቀርብ በማድረግ፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በማጠናከርና በማስፋፋት፣ የገጠር ፋይናንስ ተደራሽነትን በማስፋት፣ የመስኖ ልማት፣ ሜካናይዜሽን፣ የግብርና ማበረታቻ ሥርዓት በመዘርጋት፤ እና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ ምርታማነትን ለመጨመር ይሠራል። ግብርናችን የአየር ንብረት ተጽዕኖን የሚቋቋም እንዲሆን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የተራቆቱ አካባቢዎች በደን እንዲሸፈኑ ፓርቲያችን ይሠራል።
 3. የአርብቶ አደሩንና ከፊል አርብቶ አደሩን በሚኖርባቸው አካባቢዎች ያሉ የተፈጥሮ ጸጋዎች መሠረት በማድረግ ከሕዝቡ የኑሮ ዘዬ ጋር የተጣጣም የተቀናጀና ዘመናዊ የአርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች አከባቢ ልማት በተለይም ዘመናዊ የእንስሳት ርባታና ልማት ፕሮግራም በመንደፍ ፓርቲያችን ለአርብቶ አደር ሕዘቦች ልማትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ይታገላል።
 4. ኢንዱስትሪ የጠንካራና ዘመናዊ ኢኮኖሚ መሠረት እንደመሆኑ ዘርፉ በሀገራችን ኢኮኖሚ የሚሸፍነው ድርሻ እንዲሰፋ ፓርቲያችን በቁርጠኝነት ይሠራል። የኢንዱስትሪ ልማታችን ዋነኛ መርሕ ኤክስፖርት መር ይሆናል። ሆኖም ግን ፓርቲያችን ሀገራችን የምታስገባቸውን የውጭ ሸቀጦች በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ፖሊሲን የውጭ ንግዳችንን ከማሳደግ ጋር አስተሣሥሮ ይተገብራል። ይህም እንዲሆን ዘርፉ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ጠንካራ የኋልዮሽና የፊትዮሽ ትሥሥር እንዲኖረው የሚያደርግ፣ ምርታማነት፣ ጥራት፣ ተወዳዳሪነትን የሚያሳደግ አቅጣጫን ይከተላል። የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማፋጠን የግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፉን ትሥሥር የሚያጠናክርና ሀገራችንን በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀዳሚ ማዕከል እንድትሆን የሚያስችሉ ሥራዎችን በስፋት ይሠራል። ስለሆነም ዘርፉን ለውጭ እና ለሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ሳቢ፣ ትርፋማና አዳጊ ሊያደርጉ የሚችሉ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ፣ ምቹ የኢንቨስትመንትና ንግድ ከባቢን በመፍጠር እና የኢንዱስትሪ ሰላም በማስፈን ጠንካራ የኢንዱስትሪ ክፍለ ኢኮኖሚ ለመገንባት ፓርቲያችን ይሠራል። ፓርቲያችን ግብርናን መሠረት ላደረጉ ኢንዱስትሪዎች፣ ለሰፊ የተማረ የሰው ኃይል ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እና በስፋት ገቢ ምርቶችን መተካት የሚያስችሉ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ የሚያደርግ አቅጣጫን ይከተላል፡፡
 5. ሀገራችን ያላትን የማዕድን ሀብት በልክ እና ቀጣዩን ትውልድ በማያራቁት መልኩ ለመጠቀም የማዕድን ጥናት፣ ፍለጋ እና ማውጣት እንዲሁም ለገበያ ማቅረብ ላይ ባለሀብቶች በተለይም የሀገር ውስጥ ባለ ሀብቶች በተናጠልም ይሁን ከመንግሥት ጋር በመተባበር እንዲሳተፉ ፓርቲያችን ሁኔታዎችን ያመቻቻል። የማዕድን ፍለጋ እና የማውጣት ሥራ ዘመናዊ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ የደኅንነት ሥጋት የማይጥል እንዲሁም ከልማቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነቱንም የሚያረጋግጥ እንዲሆን ፓርቲያችን ይሠራል። 
 6. የአገልግሎት ዘርፍ በባህሪው በአንድ በኩል በራሱ እንደ ኢኮኖሚ ዘርፍ የሥራ ዕድልና ሀብት የሚፈጥር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ከፍተኛ የሆነ የአስቻይነት ሚና ይጫወታል። በመሆኑም ፓርቲያችን ሀገራችን ከአገልግሎት ዘርፉ መንትያ የኢኮኖሚ ጥቅም ተጠቃሚ እንድትሆን ይሠራል። በዚህም ረገድ የቱሪዝም ዘርፉን በማልማት እና በማዘመን እንዲሁም የቱሪዝም አማራጮችን በማስፋት ሀገራችን በአፍሪካ ካሉ ዋና ዋና የቱሪስት መዳራሻዎች አንዷ እንድትሆን ፓርቲያችን ጠንክሮ ይሠራል። ይህንንም ለማድረግ የሀገራችንን ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ሰው ሠራሽ መስሕቦችን የማስተዋወቅ እንዲሁም ለቱሪስት ፍሰትና ቆይታ ወሳኝ የሆኑ አገልግሎቶችን የሚያሳድጉ እና ለቱሪስት ምቹ የሚያደርጉ፣ የቱሪዝሙን ዘርፍ የሚያዘምኑ ሥራዎችን ነድፎ ይንቀሳቀሳል። 
 7. ፓርቲያችን የኢኮኖሚ ሴክተሮችን ውጤታማነትና ቅልጥፍና ለማሳደግ የሎጅስቲክስ እና መሠረተ ልማት አቅርቦትን በማሟላት ፈጣን፣ ውጤታማና ቀልጣፋ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ትሥሥር እንዲኖር ይሠራል፡፡ ሀገራችን የባሕር በር አልባ በመሆኗ የሚያጋጥሙ የወደብ አገልግሎት ችግሮችን ለመፍታት እንዲቻል ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ ወጥ የሆኑ ሥርዓቶች እንዲተገበሩ በማድረግ፣ የባሕር ወደብን በጋራ የማልማት እንዲሁም አገልግሎት የመስጠት ኢንቨስትመንቶች ላይ ተሳትፎ በማደርግ የሀገራችንን ጥቅም ለማስከበር ፓርቲያችን ይታገላል።

 2. ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ልማት እና ምርታማነትን መሠረት ያደረገ ማኅበራዊ ፍትሕ ማረጋገጥ

 1. የምናስመዘግበው የኢኮኖሚ ዕድገት ጠቅላላ ሀገራዊ ምርትን ከማሳደግ ባሻገር የሕዝቦችን ሰብአዊ ልማት የሚያመጣ መሆን እንዳለበት ፓርቲያችን ያምናል። በመሆኑም ለሁሉም የኢኮኖሚ ተዋንያን ፍትሐዊ እና በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተመጣጣኝ የዕድገት ዕድልን የሚፈጥር፣ የዕድገት ምጣኔው እየሰፋና ግለቱን ጠብቆ የሚዘልቅ፣ ጥራቱን የጠበቀና በቀጣይ ትውልድ ኪሣራ ላይ የማይገነባ መሠረተ ጽኑ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ፓርቲያችን ይሠራል።
 2. ፓርቲያችን መንግሥት መር ሆኖ የቆየውን ዕድገት ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የሚኖረውን ሚና አሁን ከሚገኝበት አነስተኛ ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ አስፈላጊው ሁሉ ያደርጋል፡፡ የምናስመዘግበው የኢኮኖሚ ዕድገት ጥራት ያለው፣ የአካታችነት እና የዘላቂነት ችግሮችን የሚቀርፍ፣ ምርታማነትን የሚያረጋገጥ እንዲሁም ከከፍተኛ የዕዳ ጫና የተላቀቀ እና ጤናማ የፋይናንስ ሂደትን የተከተለ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓትን እንዲገነባ ይሠራል። በተጨማሪም አርሶና አርብቶ አደሮችን፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎችን፣ ሴቶችና ወጣቶችን ከኢኮኖሚ ዕድገቱ በተጨባጭ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ይተገብራል። 
 3. ልማትን የሚያሳልጥና በየደረጃው ለሕዝቡ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ የሚሆን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መሠረተ ልማት መኖር ለሀገራችን በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ፓርቲያችን በጥብቅ ያምናል፡፡ በዚህም መሠረት በመንግሥት፣ በመንግሥትና በግል ባለ፤ ሀብት ትብብር እና በግል ባለ ሀብት ሙዓለ ነዋይ፣ ጥራት ያላቸው መሠረተ ልማቶች እንዲገነቡና በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ፓርቲያችን በጥብቅ ይሠራል፡፡
 4. ፓርቲያችን በፌደራል ሥርዓቱ ማሕቀፍ የበጀት ድልድል፣ የመሠረተ ልማትና የማኅበራዊ ልማት ግንባታና ድልድል እንዲሁም ማንኛውም የሀብት አጠቃቀም የሁሉንም ሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ ሁኔታ እንዲፈጸም ይሠራል።
 5. ፓርቲያችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ከአካባቢ ጋር የተስማሙና የብዝኃ ሕይወት ሚዛንን የጠበቁ እንዲሆኑ የሚያስችል የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተግባራዊ ያደርጋል። በዚህም በተፈጥሮ ሀብት የታደለችው ሀገራችን በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያደርጋትን የዝቅተኛ ካርቦን ልቀት እና የታዳሽ ኃይል ልማት ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲያድግ በማድረግ በሀገራችን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እንዲያብብ ይሠራል።
 6. በሁሉም አካባቢዎች ያሉ የልማት ጸጋዎችን በማልማት እንዲሁም በአንጻራዊነት በልማት ወደ ኋላ ለቀሩ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት የተመጣጠነና ፍትሐዊ ልማት በሁሉም አካባቢዎች እንዲረጋገጥ ፓርቲያችን ይታገላል፡፡
 7. ፓርቲያችን በተለያዩ ሀገራትና ዓለም ክፍሎች ከሚፈጠሩ የኢኮኖሚ ቀውሶች የሚመጡ ጫናዎችን የሚቋቋም የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲሁም የኢኮኖሚ ነጻነት ያለው ሀገራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት ይሠራል። ይህንንም ለማድረግ ፓርቲያችን ሀገራዊ ፍላጎት እና አቅርቦትን ለማጣጣም ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል። ይህም ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚረዳ ሰፊ የገበያ ፍላጎትን መፍጠር ብሎም የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ሆኖ ውጤታማ የማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያ፣ የፖሊሲ ቀረፃ እና ማስፈጸም ላይ የሚያጠነጥን የዐቅም ግንባታ ላይ አተኩሮ ይሠራል።
 8. የፋይናንስ ዘርፉ በቆጣቢ እና በኢንቨስተር የኢኮኖሚ አሐዶች መካከል የሚኖርን የገንዘብ መጠን ፍላጎት በማስታረቅ ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል። ስለዚህም ዘመናዊ አሠራርና ተወዳዳሪነት የሰፈነበት መሠረታዊ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የፋይናንስ ዘርፍ እንዲኖር ይታገላል። ይህም ሲሆን በሁሉም የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አካታች የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት በማስፋፋት እና ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ የዜጎችን የኢኮኖሚ ዐቅም ማጎልበት ላይ ትኩረት በማድረግ ይሠራል።

 1. ሀብት ፈጠራን የሚያሳድግ ዕውቀት መር ኢኮኖሚ መገንባት

 1. ዘላቂ እና አስተማማኝ ብልጽግና የሚረጋገጠው ኢኮኖሚው ዕውቀትን እንደ ግብዐትም ሆነ እንደ ምርት የሚጠቀም ሆኖ ሲገነባ እንደሆነ ፓርቲያችን ይገነዘባል። በመሆኑም በቴክኖሎጂ ዕድገት፣ በኢኖቬሽን እና በሰው ኃይል ልማት ላይ ያተኮረ የዕድገትና የልማት አቅጣጫ ከረጅምና መካከለኛ ጊዜ አኳያ መፈጸም ዋነኛ የፓርቲያችን ኢኮኖሚ ግብ አድርጎ ይንቀሳቀሳል።
 2. በሀገራችን ቀጣይነት ላለው ምርታማነትን እና የሕዝብ ኑሮ ደረጀ ለማሻሻል ቁልፍ የሆነው ዕውቅት እና ሳይንሳዊ ምርምር ዝቅተኛ ደረጃ በመሆኑ እንደሆነ ይገነዘባል። በመሆኑም ፓርቲያችን ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ቴክኖሎጂ፣ የቢዝነስ ፈጠራ እንዲሁም በዘመናዊ የአመራርነት ክሂሎቶች እና በተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ያደርጋል።
 3. ፓርቲያችን ዕውቀት መር ኢኮኖሚ የሚገነባው ለሰው ኃይል ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ነው ብሎ ያምናል። በመሆኑም በተወዳዳሪ፣ በምርታማና፣ በጤናማ የሰዉ ኃይል ልማት ላይ ትኩረት ያደርጋል። የኢኮኖሚዉን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበና ገበያን መሠረት ያደረገ የሰዉ ኃይል ልማት ስትራቴጂን ተግባራዊ በማድረግ ብቁ እና ውጤታማ የሰው ኃይል በማልማት በዕውቀት የሚመራ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ፓርቲያችን ይሠራል።

 4. ከተሜነት እና የከተማ ልማትን ማስፋፋት

 1. ፓርቲያችን በፌደራል ሥርዓቱ ማሕቀፍ የበጀት ድልድል፣ የመሠረተ ልማትና የማኅበራዊ ልማት ግንባታ ድልድል፣ እንዲሁም ማንኛውም የሀብት አጠቃቀም፣ የሁሉንም ሕዝቦች ፍትሕዊ ተጠቃሚነትና ቅልጥፍናን (efficiency) ባረጋገጠ ሁኔታ እንዲፈጸም ይሠራልⵆ የገጠር ልማትንና የከተማ ልማትን በማቀናጀትና በማስተሣሠር ዜጎች በያሉበት በሀገራዊ ልማቱ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና ፍትሐዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥና እንዲሁም ከግብርና ልማት ወደ ኢንዱስትሪ ልማት የሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር እንዲፋጠን ከተሜነትን ለማስፋፋት ይታገላል። እንዲሁም የገጠር ማዕከላት፣ የገጠር ልማትንና የከተማ ልማትን በማስተሣሠር ለመዋቅራዊ ሽግግር አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ይሠራል። የከተሞችን ሽፋን ዓለም አቀፋዊ ስታንዳርዱን ጠብቆ የከተማው ነዋሪ ድርሻ ከገጠሩ የሚኖረው ምጥጥን  ከፍ እንዲል ይሠራል፡፡ 
 2. ፓርቲያችን ከተሞች ጽዱ፣ ለኑሮ ምቹና አረንጓዴ እንዲሆኑ የተቀናጀ የከተማ ልማትን ፕሮግራም ነድፎ ይሠራል፡፡ ከተሞች የተቀናጀ የከተሞች መሠረተ ልማቶችን አቅርቦት እንዲያገኙ፣ ሞያዊ ብቃትን መሠረት ያደረገ ጠንካራ የከተማ አስተዳደር እና የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖራቸው በማስቻል መሠረታዊ የሆኑ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች ቀልጣፋ፣ጥራት ያላቸው እና የሕዝብን ፍላጎት የሚያረኩ እንዲሆኑ ፓርቲያችን ይሠራል። 
 3. ዘመናዊና የከተሞችን የዕድገት ሁኔታ ያገናዘበ የመሬት ልማትና አስተዳደር የመረጃ ሥርዓት በመዘርጋት የከተማ መሬት አቅርቦትንና አጠቃቀም ግልጽ፣ ልማትን የሚደግፍ እና ቀልጣፋ እንዲሆን ይደርጋል።
 4. ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፤ በግል ዘርፍ ሰፊ ተሳትፎ የከተማ ቤት ልማትና አስተዳደር ሥራዎችን ማጠናከርና የተቀናጀ የከተሞች መሠረተ ልማቶችን ያቀርባል።
 5. ፓርቲያችን ከተሞችን ከከተሞች እንዲሁም ክልሎችን ከክልሎች በሚያዋስኑን ሥፍራዎች በጥናት ላይ የተመሠረቱ የኢኮኖሚ ትሥሥርንና የልማት ኮሪደሮችን በማልማት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ይታገላል::
 6. ለኢኮኖሚው ከፍተኛ ድርሻ ያለውን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትንና ሕግጋትን እንዲሁም የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መንገድ ዘርፉ በገበያው ተወዳዳሪ እንዲሆን እንዲሁም ሀገር በቀል ኩባንያዎች የሚጠናከሩበትን አሠራር በመተግበር ወደ ውጤታማነት እንዲሸጋገር ይሠራል፡፡
 7. ፓርቲያችን የዜጎች መሠረታዊ ፍላጎት የሆነዉን የመጠለያ ጥያቄ ለማሟላት በተለይም በከተሞች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ቤት የሚያገኙበት አሠራር፣ የመሬትና የፋይናንስ አቅርቦቶችን ይዘረጋል፡፡ በከተሞች የመኖሪያ ቤት ልማት በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት፣ ወጭ ቆጣቢና ስፋት ያለው የቤት አቅርቦት በከተሞች እንዲኖርና የመሬት ፍጆታን በቀነሰና የወለል ከፍታን በሚጨምር መንገድ ተግባራዊ በማድረግ የቤት አቅርቦት ችግርን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ ይሠራል፡፡