የክፍለ ከተማው ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙቀት ታረቀኝ በተቀናጀ የስራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለሆኑ ነዋሪዎች ያስተላለፉት መልዕክት

የክፍለ ከተማው ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙቀት ታረቀኝ በተቀናጀ የስራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለሆኑ ነዋሪዎች ያስተላለፉት መልዕክት

  • Post author:
  • Post category:መልዕክቶች
  • Post last modified:January 24, 2021
  • Post comments:0 Comments
  • Reading time:0 mins read

እናንተ የኢትዮጵያችን ተስፋ የሆናችሁና በክፍለ ከተማችን ስራ የተፈጠረላችሁ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን! ስኬት የጥረት ምንጭ፤ የብርቱ ልፋትና ድካም ውጤት መሆኗን በጽኑ መገንዘብ አለባችሁ፡፡ ውድቀታችሁ የሚጀምረው የምትጓዙበት መንገድ ሁሉ አልጋ በአልጋ ነው ብላችሁ ማሰብ የጀመራችሁ ጊዜ ነው፡፡ በተቃራኒው ስኬታችሁ የሚጀምረው ደግሞ ነገን በዛሬ መነጽር ውስጥ አሻግራችሁ ለመመልከት ስትችሉ ነው፡፡ ዛሬ የመጀመሪያ ነገ ደግሞ የመፈጸሚያ ቀን መሆኑን ማወቅ ከእናንተ ይጠበቃል፡፡

በእነዚህ ሁለት ቀናት መካከል ያለው ሂደት ፈታኝ፤አድካሚ፤እልህ አስጨራሽና ውጣ ውረድ የበዛበት እንደሚሆን ሁልጊዜም ማሰብ ይኖርባችኋል፡፡ እናንተ ግን ለሚገጥማችሁ ማንኛውም ተግዳሮት እጅ አትስጡ፡፡ ውድቀትን እንቢ በሉ፡፡ ስኬትን ወደ እናንተ የሚያመጣውን በር ለመክፈት ብቻ ተንደርደሩ፡፡ በማሸነፍ ነገአችሁን ብሩህ ለማድረግ በሚያስችል ቁርጠኝነት ከተሰማራችሁ የሚያቅታችሁ አንዳችም ነገር እንደማይኖር ለአዕምሮዋችሁ ደግማችሁ ደጋግማችሁ ንገሩ፡፡

ዛሬ እኛ የሰጠናችሁ የህይወታችሁን የመጀመሪያ ፊደል ‹‹ሀ››ን እንጂ የህይወታችሁን የመጨረሻ ማብቂያ ‹‹ፐ››ን አይደለም፡፡ ከመጀመሪያው ፊደል ተነስቶ የመጨረሻው ጋር ለመድረስ በመካከላቸው ያሉትን 30 ፊደላት ማለፍ የግድ ይላል፡፡ ህይወትም እንዲሁ ናት፡፡ 30 አይነት ውጣ ውረድ፤30 አይነት መሰናክል አለባት፡፡ ይህን በጽናት ያለፈ ከመራርነቷ ባሻገር ያለውን ጣፈጭ ፍሬ ለመቅመስ ይችላል፡፡ ውጣ ውረዱን ማለፍ ተስኖት በየመንገዱ የተንጠባጠበ ግን በእሾህ መካከል እንደበቀለ ዘር ጠውልጎ ይቀራል፡፡ ምርጫው አንድና አንድ ነው፡፡ መድከም፤መትጋት፤መልፋት፤መውደቅና መነሳት በመጨረሻም ከስኬት ማማ ላይ መውጣት፡፡


ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን

እኛ እዚህ የተገኘነው በፍጹም የአገልጋይነት መንፈስ እናንተን ለማገልገል ነው፡፡ እኛ እዚህ የተገኘነው የእናንተን የህይወት ጎዳና ለማቅናት ነው፡፡ የዘወትር ሃሳባችንም ሆነ ተግባራችን በኢኮኖሚ አቅማችሁ ዳብራችሁ ለእራሳችሁ፣ ለቤተሰቦቻችሁና ለአገራችሁ እንድትጠቅሙ ማድረግ ነው፡፡ ምንዳችንም የእናንተ ለውጥ፤የእናንተ ደስታና እርካታ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ዛሬ ባገኛችሁት እድል ተጠቅማችሁ ልፋታችንን ከውጤት ድካማችንንም ከስኬት እንድታደርሱልን ትጠየቃላችሁ፡፡ በሰበብ አስባቡ ተሸብባችሁ በየፌርማታው እንድትቀሩ አንፈቅድም፡፡ የሚገጥማችሁን ማናቸውንም ችግሮች ከእናንተ ጎን ቆመን ለመፍታም አንቦዝንም፡፡ ጀምራችሁ እስከምትጨርሱ ድረስም ከአጠገባችሁ አንለይም፡፡ በሁሉም ሂደታችሁ ከጎናችሁ ስለመሆናችን ስንነግራችሁም ለማለት ብቻ ሳይሆን በተግባር እንደምናደርገውም ስለምናውቅ ነው፡፡ እኛ ከእናንተ የምንፈልገው የመለወጥና የማደግን፤አብዝቶ የመትጋትንና ወደስኬት ጎዳና የመሻገርን፤ በስራና በስራ ብቻ የመለወጥ ሞራልንና ተነሳሽነትን ነው፡፡


ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን

ዝቅ ብላችሁ ከፍን፤ጎንበስ ብላችሁ ቀናን፤አስተውላችሁ መጀመርን፤ አስር ጊዜ ለክታችሁ መቁረጥን፤ሰከን ብላችሁ መፍጠንን ገንዘባችሁ አድርጉ፡፡ በትንሽ ውጤት እንዳትሰክሩ፤በብዙው ትርፍም እንዳትኮሩ፡፡ዛሬ የምትነሱበትን መሰረታችሁን በማጽናት ከትንሽ ወደ ትልቅ ከጥቂት ወደ ብዙ ለመሻገር እንጂ የአቋራጭ መንገድን ለመጠቀም ፈጽሞ እንዳትሞክሩ፡፡ የአቋራጭ መንገድ ምናልባት ዛሬ እንጂ ነገን አያሻግርም፡፡ አቋራጭ መንገድ እንደ ቀትር ጥላ ነው፡፡ ጸሐይ ስትጠፋ እሱም አብሮ ይጠፋል፡፡ ጠመዝማዛውና አሰልቺው መንገድ ግን መዳረሻው ዘላቂ ደስታና እርካታ ነው፡፡ እናንተም በእዚህኛው መንገድ በመጓዝ ከህይወታችሁ ስኬት እንድትደርሱ አደራ እላለሁ፡፡
አመሰግናለሁ!!

Leave a Reply