አቶ ብርሃኑ አበራ
የኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ክተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ መልዕክት
ውድ የክፍለ ከከተማችን የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች፤አባላትና ደጋፊዎች ፓርቲያችን ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ እያስመዘገባቸው ያሉ በርካታ ውጤቶች ለአገራችን ሁለንተናዊ የለውጥና የብልጽግና ጉዞ ስኬት ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን እንደምትገነዘቡ አምናለሁ፡፡ ምንም እንኳን ባለፉት የለውጥ አመታት የመጣንበት መንገድ እጅግ ሲበዛ ውስብስብ ቢሆንም ወደኋላ ላይመለስ የተቀጣጠለውን አገራዊ ለውጥ ለማቆም የሚያስችለው አንዳችም ኃይል ግን አልተገኘም፡፡ ትናንት በአንድ ማዕድ አብረውን እጃቸውን የሰደዱቱ ቢከዱንና በለውጥ ጉዟችን ላይ አደጋ ለመጋረጥ ቢሞክሩም ለውጡ በኢትዮጵያዊ የአንድነት መንፈስ እንዲጎመራ አደረጉት እንጂ ከቶውንም ሊያስቆሙት አልቻሉም፡፡
ጥቂት የማይባሉ የውስጥ ባንዳዎች ከባዕዳን ጋር አብረው ከጀመርነው የእድገት ጉዞ ሊያደናቅፉን ቢሹም እኛ ግን ከልባችን እየተጋን፤አፍራሽ አስተሳሰቦችን እየታገልን መጪውን ጊዜ የኢትዮጵያችን ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን፡፡ ይህ ሂደት አድካሚና እልህ አስጨራሽ ቢሆንም ከመላው የፓርቲያችን አመራር፤ ከአባላችንንና ከደጋፊዎቻችን ጋር በጋራ በመሆን እንደምንወጣው ዕምነታችን ጽኑ ነው፡፡ መላው የፓርቲያችን አመራሮች ብልጽግና በአንድ ጀንበር የሚረጋገጥ፤ እዚህ ጋር ሲደርስ ይበቃል አልያም ሆኗል፤ አልቋል የምንለው አይደለም፡፡ በበርካታ ውጣ ውረዶች የታጀበ ሂደት እንጂ፡፡ ይህን የአቀበትና የቁልቁለት፤በበርካታ ተግዳሮቶች የተከበበ ሂደት በትዕግስትና በጠንካራ ትግል ማለፍን ይጠይቃል፡፡ በአንድነትና በአብሮነት በወንድማማችነትና በጋራ አስተሳሰብ የተቃኘ ከእኔ ወደ እኛ የተቀየረ አስተሳሰብን ይጠይቃል ብልጽግና፡፡
ፓርቲያችን በመነቃቀፍ ሳይሆን በመደጋገፍ በመገፋፋት ሳይሆን በመተቃቀፍ ላይ የተመሰረተ አካሄድ ኢትዮጵያን ያሻግራል የሚል ጽኑ ዕምነት አለው፡፡ በመሆኑም በአንድ ጥላ ውስጥ የቆምን ግን በየፊናችን የተጠመድን፤ ለጋራ ዓላማ የተሰለፍን ግን በየግላችን የምንኳትን ከመሆን መውጣት አለብን፡፡ አገርን የሚያሳድገው የጋራ ተሳትፏችን እንጂ በየግል ስሜቶቻችን መሮጥ አይደለም፡፡ ሁላችንም ‹‹እኔ ለአገሬ ምን አደረኩላት እንጂ አገሬ ለኔ ምን አደረገችልኝ?›› አንበል፡፡ አገርን ለማሳደግ በሚጠቅመው አሻራችንን ማሳረፍ ላይ ማተኮር ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባራችን መሆን አለበት፡፡
ብልጽግና የሁሉንም ትብብርና ድጋፍ የሚሻ የመለወጥ፤የማደግና ከኃያላኑ ተርታ የመሰለፍ ጉዞ ነው፡፡ ይህ አድካሚ ጉዞ በግል በመሮጥ ብቻ የሚሳካ አይደለም፡፡ ብልጽግና ሊሳካ ከሆነ የጋራችን ርብርብ የግድ ይላል፡፡