- የውጭ ግንኙነት ዋና ዓላማ፡– ሀገራዊ ክብርን ማዕከል ያደረገ የውጭ ግንኙነት
ፓርቲያችን የውጭ ጉዳይን ከሀገር ውስጥ ጉዳይ የተነጠለ አድርጎ አይመለከትም። ይልቁንም የሀገር ውስጥ ጉዳያችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጦች ነፀብራቅ ሆኖ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ያልዘነጋ ነው። የውጭ ግንኙነታችንም የዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታን የሚያረጋግጥ፤ የሀገር አንድነትን በማስጠበቅ ሀገራዊ ክብርን የሚያጎናጽፍ፤ ሀገራዊ ክብርን በማጎናጸፍ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ይሆናል። ሀገራዊ ክብር የሌለው ሀገር ሀገራዊ ጥቅሙን ሊያስጠብቅ እንደማይችል ፓርቲያችን በጥብቅ ይገነዘባል። በመሆኑም የኢትዮጵያን ታሪክ እና አንድነት እንዲሁም የዜጎቿን ክብርና ተስፋዋን የሚያንፀባርቅ የጋራ ስምምነት ያለው ሀገራዊ ክብርን እና ሀገራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠብቅ የተቀናጀና የተማከለ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ትግበራን እውን ያደርጋል። ሀገራዊ ክብራችንን ለማረጋገጥ እና ጥቅሞቻችንን ለማስከበር፣ አስቀድሞ ግንኙነትን በማደስና በማጠናከር ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ትኩረት በማድረግ በግንኙነት ብልሽት ምክንያት የምናጣቸውን ሀገራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስከበር አመች ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ በውጭ ግንኙነት መስክ ሀገራችን መልካም የሚባል ውጤት ያስመዘገበች ሀገር ብትሆንም የውጭ ግንኙነታችን ከጉድለት እና ከግድፈት የጸዳ አይደለም። ስለዚህ ግድፍቶቹን እና ጉድለቶችን መለየት፣ ማስተካከል እና መሙላት እንዲሁም የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን ማስቀጠል የፓርቲያችን የውጭ ግንኙነት መሠረቶች ናቸው።
- የውጭ ግንኙነት ግቦች
- ሀገራዊ ክብርን የሚያረጋግጥ የውጭ ግንኙነት
- ፓርቲያችን የዜጎቻችን ክብር የሀገራዊ ክብራችን ዓይነተኛ መገለጫ እንደሆነ ይገነዘባል። በመሆኑም ዜጎቻችን በየትኛውም የዓለም ክፍል ቢሆኑ ክብራቸውን የሚያስጠብቅ የውጭ ግንኙነት ሥራ የፓርቲያችን የውጭ ግንኙነት መርሐ ግብር ቁልፍ መርሕ ነው፡፡ ፓርቲያችን የዜጎችን ክብር መሠረት ያደረገ ሀገራዊ ክብርን ለማስጠበቅ ዜጎችን መሠረት ያደረገና የዜጎችን መብት በየትኛውም የዓለም ክፍል ሊያስጠብቅ የሚችል የውጭ ግንኙነት ሥራዎችን ይተገብራል።
- ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍላት ሥራ ፍለጋ ይሰደዳሉ። በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ለሥራ የወጡ ዜጎቻችንን ደኅንነት፣ ክብር እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ታሳቢ ያላደረገ የውጭ ግንኙነት የኢትዮጵያን ክብር ሊያስጠብቅ ስለማይችል ፓርቲያችን በውጭ ግንኙነት እነዚህን ዜጎቻችንን ታሳቢ ያደረገ ሥራን ይሠራል። የሀገራችን ዜጎች ከውጭ የሥራ ቅጥር የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆኑበት እና መብቶቻቸውና ክብራቸው የሚጠበቅበት ሁኔታ ከቀጣሪ መንግሥታት ጋር ስምምነትን በመፍጠር እንዲመቻች ያደረጋል።
- የሀገራችንን መልካም ገጽታና የወደፊት ብሩህ ተስፋ ለውጭው ዓለም የሚያስተዋውቁ የውጭ ግንኙነት ሥራዎች ይሠራሉ።
- የፓን-አፍሪካኒዝም መሠረት የሆነችው ሀገራችን መላው ጥቁር ሕዝቦች የሚያከብሩትና የሚያምኑትን ያህል ፓን-አፍሪካኒዝምን የሚያጠናክር የውጭ ግንኙነት ሥራዎችን መተግበር ይኖርባታል። ፓርቲያችን ይህን በመረዳት የፓን-አፍሪካኒዝም መሠረትነታችንን የሚያጎሉ ሥራዎች እንዲተገበሩ ያደርጋል።
- ለትብብርና ለጋራ ተጠቃሚነት ትኩረት በመስጠት አጋሮቻችንን ማስፋት
- ፓርቲያችን የተሻለው መንገድ በትብብርና ፉክክር መሐል ሚዛን መጠበቅ እንጅ ያልተገባ ፉክክር ተገቢ እንዳልሆነ ያምናል፡፡ የውጭ ግንኙነታችን ፖሊሲና ትግበራ ትብብርን፣ የጋራ ጥቅምን እና ሉዓላዊነትን በማስከበር እና በማክበር ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ያምናል፡፡ ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ ሀገራዊ ጥቅምን ለማስከበር ቀዳሚው ነገር ግንኙነትን ማደስ እንደሆነ ያምናል። በመሆኑም በፉክክር እና በመቀናቀን ከሚመጣ አንጻራዊ ጥቅም ይልቅ ከውስጣዊ ፍላጎታችን የሚመነጭ ጥቅምን የሚያስቀደም የውጭ ግንኙነት በመከተል አጋሮቻችን ለማስፋትና ግንኙነትን ለማጠንከር አበክሮ ይሠራል፡፡
- የምንኖርበት ዓለም ባለ ብዙ ዋልታ እንደመሆኑ ከየትኛውም ዋልታ ዲፕሎማሲያዊ ጥግ ሳንይዝ በዋልታዎች መካከል ዲፕሎማሲያዊ ሚዛንን በመጠበቅ ሀገራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር ይሠራል። ዲፕሎማሲያዊ ሚዛንን በመጠበቅ ከነባር አጋሮች ጋር የነበረ ግንኙነት እንዲጠናከር ከመሥራት ባሻገር ከአዳዲስ አጋሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ይደረጋል፡፡
- የብዙዮሽ ትብብር ተቋማት ተሰሚነትን መጨመር እና ፓሊሲያዊ ነጻነትን ማስከበር
- የብዙዮሽ ዲፕሎማሲን በመጠቀም ዓለም አቀፍ ተሰሚነታችንን ማሳደግ እና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሉዓላዊነታችንን የጠበቀ መልካም ግንኙነትን ለመፍጠር ፓርቲያችን ይሠራል፡፡ የፖሊሲ ነጻነታችንንና ሉዓላዊነታችንን ባስጠበቀ መልኩ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የባለ ብዙዮሽ ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች ይሠራል። ሀገራችን በብዙዮሽ ዲፕሎማሲ የአፍሪካ ድምፅ በመሆን የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል እንድትሆን ያላሰለሰ ጥረት ያደረጋል።
- ለጎረቤት ሀገራት ትኩረት በመስጠት ዘርፈ ብዙ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ
- ሀገራችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በመፍጠር አካባቢያዊ ሰላም እንዲረጋገጥ ፓርቲያችን በትኩረት ይሠራል። የአካባቢያዊ ሰላም ችግር የሆኑ ሽብርተኝነትና ሌሎችም የሰላም ጠንቅ የሆኑ ጉዳዮችን ለመግታት ከጎረቤትና ሌሎች ሰላም ወዳድ ሀገራት ጋር በመሆን በቅንጅት ይሠራል። በተጨማሪም ለአካባቢያዊ ሰላም መደፍረስ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ በጎረቤት ሀገራት መካከል ያሉ መልካም ያልሆኑ ግንኙነቶች እንዲሁም በጎረቤት ሀገራት ውስጥ ያሉ አለመግባባቶች ቀጣናዊ ችግሮችን ከመፍጠራቸው በፊት በሰላማዊ መልኩ መግባባት እንዲፈጠርባቸው የማግባባት ሥራዎች ይሠራል፡፡
- በቀጣናው ካሉ ሀገሮች ጋር የጋራ ጥቅሞቻችንን መሠረት ያደረገ አካባቢያዊ የልማት፣ የኢኮኖሚ እና የሰላም ትሥሥር እንዲፈጠር በትብብር ይሠራል። ይህም ቀስ በቀስ እያደገ የሚሄድ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትሥሥር እንዲሆን አስፈላጊውን ጥረት ያደርጋል። ይህንንም ለማድረግ በቀጣናችን ያሉ ነባር አካባቢያዊ ድርጅቶች እንዲጠናከሩ ለማድረግ እንዲሁም ድርጅቶቹ ለቀጣናዊ ትሥሥር መፈጠር መሠረት እንዲጥሉ በትኩረት ይሠራል፡፡ በተጨማሪም እነዚህ አካባቢያዊ ድርጅቶች የቀጣናው የተበታተኑ ድምፆች ወደ አንድ መሰባሰቢያ በማድረግ የቀጣናው ሀገራት የመደራደሪያ ዐቅም እንዲሆኑ ጥረት ያደርጋል፡፡
- ከጎረቤቶቻችን ጋር በሚያገናኙን የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ በጋራና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርሕ የሀገራችንን ጥቅም ለማስከበር ፓርቲው ይሠራል። ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችንን የመጠቀም መብታችንን ባከበረ፣ ዓለም አቀፍ የድንበር ተሻገሪ ወንዞች መርሖችን በተንተራሰ መልኩ ለጥቅም እንዲውሉ ደረጋል። እንዲሁም በአጠቃቀም ምክንያት የሚመጡ አለመግባባቶችም በዓለም አቀፍ መርሖችና በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች እንዲፈቱ በዘላቂነትም በወንዞቹ ላይ ሁሉን አቀፍ የሆነ ስምምነት እንዲዳረስ ያደረጋል። በተመሳሳይ ሀገራችን በአካባቢያችን ካሉ ባለ ወደብ ሀገሮች የተሻለ የወደብ ተጠቃሚነት መብት በሚያረጋግጥ መልኩ አካባቢያዊ ትብብሮች ላይ ትኩረት በመስጠት እንዲሠራ ያደረጋል።
- የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ ማሳደግ
- ከሀገራቸው ጋር የተለየ ቁርኝት ያላቸው በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሁኔታዎች የተነጠሉ እንዳይሆኑና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። በዚህ ጉዳይ ኤምባሲዎቻችን ከምንም ጊዜ በላይ በውጪ ላሉ ዜጎች እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቅርብ ይሆናሉ። ለመብቶቻቸው ቀድሞ ደራሽና ጠበቃ፣ ለደኅንነታቸው ቀዳሚ ዋስትና እንዲሆኑ ይደረጋል።
- በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ባለቤት እንዲሆኑ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር በየሚኖሩበት ሀገር የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እንዲሆኑ በማበረታታት ላይ በትኩረት ይሰራል።
- ሀገራዊ ክብርን እና ሀገራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ የውጭ ግንኙነት የመፈጸም ዐቅም መገንባት
- ፓርቲያችን የኢትዮጵያን ታሪክ እና አንድነት አንዲሁም የዜጎቿን ክብር እና ተስፋዋን የሚያንፀባርቅ የጋራ ስምምነት ያለው ሀገራዊ ክብራችንን እና ሀገራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠብቅ የተቀናጀ እና የተማከለ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ትግበራ እውን ይደረጋል፡፡ የውጭ ግንኙነት ተቋሞቻችን የውጭ ግንኙነትን የማስፈጸም ዐቅማቸው የላቀ እንዲሆን የመምራት ዐቅም ባላቸው አመራሮችና የመፈጸም ብቃት ባላቸው ባለሞያዎች እንዲዋቀሩ ያደረጋል። አምባሳደሮቻችን የሀገራችንን ስምና ክብር እና የኢትዮጵያን አንድነት የሚያንጸባርቁ መሆናቸውን ፓርቲያችን ያምናል፡፡ በመሆኑም አምባሳደሮች ሀገራችንን እና ታሪኳን ጠንቅቅው የሚያውቁ እና ሀገራዊ ክብራችንን የሚያስጠብቁ፣ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ዕውቀት ያላቸው እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም የውጭ ግንኙነት ዘርፉና ተቋማት ወቅቱን ባገናዘበ ሀገራዊ ሁኔታዎች እና ዓለም አቀፍ ዕድገቶች በተቃኘ መልኩ እንዲያድጉ እና እየተለወጡ እንዲመጡ ይሠራል፡፡
- የውጭ ግንኙነት ማስፈጸሚያ ሀገራዊ ዐቅማችን በገር ኃይል ዐቅማችን ላይ እንዲመሠረት ሰፊ ጥረት ያደረጋል። ይህም ካለን ወረት በተጨማሪ በቀጣይ በሚከናወኑ የመልካም ገጽታና አዎንታዊ ተጽዕኖ የመፍጠሪያ ተግባራት በመነሣት እየተገነባ የሚሄድና ከጎረቤቶቻችንም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ጋር በምንፈጥረው መተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እየዳበረ የሚሄድ ይሆናል። ለዚህም በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል።
- የሀገራዊ ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ ጉዳይ በገር ኃይሎች ዐቅም ብቻ የሚመለስ ባለመሆኑ ሀገራዊ ክብራችን ሳይደፈር የመግታት ዐቅም ያለው ጠንካራ፣ ዘመናዊና ሁሉን አቀፍ ወታደራዊ ኃይል መገንባት ይገባል ብሎ ፓርቲያችን ያምናል። በመሆኑም የመከላከያ ዐቅማችን የዘመኑን ዐውደ ውጊያ የዋጀ፣ በዋናነት ጥቃትን ከወዲሁ የማስቀረት ዐቅምን መሠረት የሚያደርግ፣ በማንኛውም መስክ የሚቃጡትን ትንኮሳዎች ለመመከት የሚችል፣ ለዜጎቻችን ኩራት በሚሆንና ሀገራዊ ጥቅማችንን በሚያስጠብቅ መልኩ እንዲደራጅ ይሠራል።
- ፓርቲያችን ሀገራዊ ክብራችንን እና ሀገራዊ ጥቅማችንን ሊያስከብር የሚችል ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲን ለመተግበር የሚያስችል ዐቅምን ከማሳደግ እና ከመተግበር ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲን በመተግበር የትብብር ዘርፎችን ለማስፋት ፓርቲያችን ቅድሚያ ሰጥቶ ይሠራል፡፡ በዚህም የሰላም፣ የኢኮኖሚ፣ የዜጋ ተኮር እና የሕዝብ ለሕዝብ(ፐብሊክ) ዲፕሎማሲ የውጭ ጉዳይ ፓሊሲ ዋነኛ መተግበሪያ ስትራቴጂዎች ሆነው እንዲሠራባቸው ትኩረት ይሰጣል። በሌላ በኩልም ለመገንባት ለምንጥረው ዕውቀት መር ኢኮኖሚ እና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ከሚፈለገው የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ፣ ብሎም ከቀደሙት ሀገራት ልምድን ለመቅሰምና የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ የሳይንስ ዲፕሎማሲን የሚያጠናክሩ ሥራዎች ይሠራሉ።
- ሀገራዊ ክብርን የሚያረጋግጥ የውጭ ግንኙነት