1. የፖለቲካ ፕሮግራማ ዓላማ:-
ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ዘላቂ ሀገረ መንግሥት መገንባት
የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም ዋነኛ ዓላማ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው፣ የብሔር ማንነትን እና የሀገራዊ አንድነትን ሚዛን የጠበቀ ሀገረ መንግሥት መገንባት ነው። ከጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ አንጻር ፓርቲያችን ሕዝብ ከቀጥተኛ የህልውና አደጋ ተጠብቆ የልማት፣ የእኩልነት እና የነጻነት ፍላጎቶቹ እንዲሟላለት የሚያስችል ነጻ፣ ገለልተኛና ብቃትን መሠረት ያደረገ ሀገራዊ ተቋማዊ አደረጃጀት መገንባት ያስፈልጋል ብሎ ያምናል። በመሆኑም የሀገረ መንግሥት ግንባታ ጅምራችን ጠንካራና የማይናወጥ ተቋማዊ መሠረት እንዲኖረው ማብቃት የብልጽግና ፓርቲ አንዱ ግብ ነው። የብልጽግና ፓርቲ ዲሞክራሲን በተቋማዊና ሕዝባዊ ባህል ላይ መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባል፡፡ በሌላ በኩል ከሀገረ መንግሥት ቅቡልነት አንጻር የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ጥንካሬን ለማሳደግ በሕገ መንግሥታችን የተቀመጠውን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር ግብ ለማሳካት ይሠራል። በመሆኑም የሀገረ መንግሥቱን ቅቡልነት በሚጨምሩና ሀገራዊ መግባባትን በሚያመጡ፣ የሕዝቦችን ግንኙነት በሚያሳልጡ እና የዕርቅ መንፈስን በሚያጎለብቱ ፖለቲካዊ እርምጃዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ይንቀሳቀሳል። ፓርቲያችን የሀገረ መንግሥት ግንባታችን ኅብረ ሀገራዊ ማንነትን የተላበሰና ብዝኃነትን የሚያንጸባርቅ መሆን እንዳለበት በጽኑ ያምናል።
2. የፖለቲካ ፕሮግራም ግቦች
2.1. ጠንካራና ቅቡል ሀገረ መንግሥት በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ሀገራዊ መግባባት መፍጠር
- የብልጽግና ፓርቲ የቆመላቸው የፖለቲካ ዓላማዎች እንዲሳኩ ፓርቲው ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው ነገሮች አንዱ የሀገራዊ መግባባት ጉዳይ ነው። ኅብረ ሀገራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓቱ ምቹ መደላድል እንዲኖር ለማድረግ፣ የሀገረ መንግሥቱን ቅቡልነትም ከፍ ለማድረግ የብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊ መግባባትን ለማዳበር በጽኑ ይሠራል።
- የብልጽግና ፓርቲ በሀገሪቱ ልሂቃን መካከል የሚታየው ዋልታ ረገጥነት እና እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ሳይቀር ያለው ቅራኔና አለመተማመን ጤናማ እንዳልሆነ ይገነዘባል። ፓርቲው የሐሳብ ልዩነቶች እንዲሁም የጥቅምና የፍላጎት አለመጣጣሞች ተፈጥሯዊ መሆናቸውን ይረዳል። እንደዚህ ያሉ ልዩነቶች አይቀሬና በዴሞክራሲ አግባብ ሊስተናገዱ ቢችሉ ጠቃሚና ገንቢ ናቸው ብሎም ያምናል። ነገር ግን ሀገራዊ ህልውናን እና ኅብረ ሀገራዊ አንድነታችንን አጠያያቂ የሚያደርጉ፣ የሀገረ መንግሥቱን ቅቡልነት የሚሸረሽሩ የከረሩ አለመግባባቶች ግን አሉታዊ ተጽዕኗቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ይገነዘባል። በመሆኑም የብልጽግና ፓርቲ እጅግ መሠረታዊ በሆኑና ለሀገረ መንግሥቱ ቅቡልነት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሰፊና ጠንካራ ሀገራዊ መግባባት እንዲዳብር ይሠራል።
- ፓርቲያችን ሀገራዊ መግባባትን ለማዳበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚሠራቸው ተግባራት አንዱ በሀገራችን የቂምና የጥላቻ ታሪክ ምዕራፍ እንዲዘጋ ማድረግ ነው። ይህን ለማሳካት ባህላዊና ዘመናዊ የዕርቀ ሰላም ግንባታ አማራጮችን በመጠቀም ዕርቀ ሰላምን ለማምጣት በቁርጠኝነት ይታገላል። ለቀጣዩ ትውልድ ቂምና ቁርሾ ሳይሆን ሰላምና ወንድማማችነትን ለማውረስ የዕርቀ ሰላም አማራጮችን ሁሉ አሟጦ ይጠቀማል።
- የሐሳብ ልዩነቶችን ለማጥበብ እና ቅራኔዎችን ለማስወገድ ፓርቲያችን በጥናት ላይ የተመሠረተ ውይይቶችን እና ሕዝባዊ ተዋሥዖዎችን የሚያስቀድሙ ድርድሮችን በተከታታይና በቀጣይነት እንዲካሄዱ በማድረግ የሀገራዊ መግባባትን ለማዳበር ይሠራል። በነጠላ ጉዳዮች ላይ የጠለቁ ውይይቶች እንዲካሄዱ በማድረግ ቅራኔዎችን ደረጃ በደረጃ እየፈቱ ለመሄድ በትጋት ይንቀሳቀሳል፡፡
- የብልጽግና ፓርቲ በሀገራችን የምንፈጥረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ኅብረ ሀገራዊ አንድነትን የጠበቀና የሁሉም ማንነቶች ነጸብራቅ የሆነ፤ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ባህልና ማንነት የጠበቀ መሆን እንዳለበት በጽኑ ያምናል። ስለሆነም የምንገነባው ማኅበረሰብ ኅብረ ሀገራዊና በአጠቃላይም ኅብረ ማንነታዊ እንዲሆን፣ ዜጎችም ብዝኃነትን የተረዱና የሚያከብሩ እንዲሆኑ አበክሮ ይሠራል።
- የብልጽግና ፓርቲ የበለጸገችና ኅብረ ሀገራዊ አንድነቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ያለ ዴሞክራሲ እውን ማድረግ አይቻልም ብሎ ያምናል። የሕዝቦች ድምር የልማት፣ የእኩልነት እና የነጻነት ፍላጎት የሚያሟላ ሁለ ገብ የሆነ ብልጽግና እንዲመጣ የዴሞክራሲ አጀንዳ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ፓርቲያችን የሕዝብ ሉዓላዊነት መከበር እንዳለበትና የመንግሥት ሥልጣን በሕዝብ ይሁንታና ውክልና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ ሊገኝ እንደሚገባ ያምናል። ዴሞክራሲ የሕዝብ ወኪሎች ከሚመረጡበት የምርጫ ሂደት አልፎ በይዘቱም የሕዝቦች እኩልነት፣ ነጻነት እና ውክልና የሚረጋገጥበት እንዲሆን ይታገላል። የብልጽግና ፓርቲ ዴሞክራሲ በትምህርት፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ በመታጀብ አሰላሳይ፣ ሞጋችና ፈጣሪ ኅብረተሰብ በመገንባት ረገድ አስተዋጽዖ ሊኖረው ይገባል ብሎ ያምናል። በመሆኑም የምንገነባው ዴሞክራሲ ተቋማዊ መሠረቱ ጽኑ እንዲሆንና ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶች የዳበሩ እንዲሆኑ ብሎም ወደ ባሕልነት ደረጃ እንዲያድጉ ፓርቲያችን ይሠራል። በሀገራችን አስተማማኝና ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተመሥርቷል ልንል የምንችለው የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በአስተማማኝና በጠንካራ ተቋማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ባህል መሠረት ላይ ሲታነጽ እና ሥርዓቱ ራሱን እያጠነከረ መደበኛ ሂደት ውስጥ በመግባት የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ብሎ ፓርቲያችን ያምናል። ይህ የማይቀለበስ የዴሞክራሲ ጉዞ ብዙ ዓመታትን ሊፈጅ የሚችልና በመሰናክሎችም የታጀበ ውጣ ውረድ ያለው መሆኑን በመገንዘብ ፓርቲያችን ጽኑ ትግል ያደርጋል።
- የምንገነባው የዲሞክራሲ ሥርዓት የግለሰብ መብቶችንና የቡድን መብቶችን ሳያበላልጥ የሚያስከብርና ሁለቱንም የመብት ዓይነቶች ለማስከበር በየባሕሪያቸው ልክ የተቀየሰ አቅጣጫን ይከተላል። ፓርቲያችን የግለሰብና የቡድን መብት ተነጣጥለው ሊሄዱ እንደማይችሉ ይገነዘባል፡፡ የግለሰብ መብትን በተሟላ መልክ ለማክበር ለቡድን መብቶችም እኩል ዕውቅና እና ትኩረት መስጠት እንደሚገባ፣ እንዲሁም የቡድን መብቶች በተሟላ ሁኔታ እንዲከበሩ ለማድረግ የግለሰብ መብቶችን ማክበር አስፈላጊ እንደሆነ ፓርቲያችን ያምናል። ይህን እውን ለማድረግም ፓርቲያችን እውነተኛ፣ ዴሞክራሲያዊ ፌደራላዊ ሥርዓት ለማጠናከር በጽኑ ይታገላል። ፓርቲያችን የፌደራል ሥርዓቱ ዋና ምሦሶ ብዝኃነትን ለማስተናገድ መቻሉ ነው ብሎ ያምናል። በመሆኑም ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዕውቅና የሰጠ ፌዴራላዊ ሥርዓት በመገንባት ኢትዮጵያ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መብት የተከበረባት እውነተኛ ኅብረ ሀገራዊት ሀገር እንድትሆን ይሠራል። በአንጻሩም የግለሰብ መብቶችን በተመሳሳይ በሕገ መንግስት ማሕቀፍ ሥር ማስከበር ይቻላል ብሎ ያምናል።
- እንደ ኢትዮጵያ ብዝኃነት በሚንፀባረቅባቸው ሀገራት በፉክክር ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን የትብብር እና የፉክክር ሚዛንን የጠበቀ የዴሞክራሲ ሥርዓት ተግባራዊ መሆን እንዳለበት ፓርቲያችን ያምናል። ስለዚህ ፓርቲያችን ለትብብርና መግባባት ትኩረት የሚሰጥ የሥልጣን ክፍፍልና ውክልና፣ እራስን በራስ የማስተዳድር ያልተማከለ ፌደራላዊ ሥርዓት እና ታላቅ ቅንጅትን መሠረት ያደረገ የጋራ አስተዳደር እንዲሁም ትንሽ ቁጥር ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች መብት በልዩ ሁኔታ የሚያስከብር አካታችና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ በማድረግ በሂደት በሐሳብ ልዕልና ላይ የተመሠረት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ይታገላል።
- ብልጽግናን ማረጋገጥ እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውጥን ያለ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ሞያዊ ብቃት ያላዳበሩ ተቋማት እውን ሊሆን እንደማይችል ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል። ስለሆነም የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራዎቻችን ለተቋማት ግንባታና አሠራር ቅድሚያ የሚሠጡና በዚያ ዙሪያ የሚያተኩሩ ይሆናሉ። ስለዚህም ፓርቲያችን የሕዝብ አስተዳደር፣ የዴሞክራሲ፣ የሰላም እና የደኅንነት እንዲሁም የሕግ አስከባሪና የፍትሕ ተቋማት እንደየባህሪያቸው ነጻ፣ ገለልተኛ እና ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ በትጋት ይሠራል። የመንግሥትና የፖርቲ አሠራሮች በሀገራችን የመደበላለቅ መሠረታዊ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ፓርቲያችን ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል፡፡
- ፓርቲያችን የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት በዴሞክራሲያዊ መሠረት ላይ የታነጹ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ለሀገር እና ለሕዝብ ጥቅም የቆሙ ወገንተኝነታቸው ለሀገር ብቻ የሆኑ ተቋማት ለማድረግ ይታገላል፡፡ በዚህም ረገድ በየተቋማቱ ያለውን የሞያ ብቃት እና ክሂሎት፣ እንዲሁም አደረጃጀት ከአካባቢው ሁኔታ እና ከዘመናችን የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር አቆራኝቶ ተቋማቱን ለማጠናከር በትኩረት ይሠራል።
- የሀገረ መንግሥቱን ጥንካሬ ለማጎልበት እንዲሁም ተቋማት የተጣለባቸውን ሕዝባዊ አደራ እና ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ሀገረ መንግሥቱ የተዋቀረባቸው ተቋማት ባህሪ እና ተልዕኮን ማዕከል ያደረገ፣ በዕውቀት የሚመራ፣ ለየዘርፉ ልዩ ባህሪ ያገናዘብ፣ ለአመራር ብቃት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ያልተማከለ የተቋማት ሪፎርም እንቅስቃሴ ፓርቲያችን ተግባራዊ ያደርጋል።
- ፓርቲያችን ማንኛውም ፖለቲካዊ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ፣ ሕጋዊ ወይም ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሕገ መንግሥትን የተከተሉ መሆን አለባቸው ብሎ ያምናል። የሕግ አውጭው፣ የሕግ አስፈጻሚው እና የሕግ ተርጓሚው የሥልጣን ከፍፍል በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆንና የእርስ በርስ ቁጥጥርና ሚዛን እንዲጠናከር፣ የመንግሥት አካላት ተጠያቂነትን እንዲረጋገጥ፣ ሕግ አውጭውን የሚያጠናክሩና የዳኝነት አስተዳደሩን የሚያጎለብቱ አሠራሮች እንዲዘረጉ ያደርጋል። ፓርቲያችን ሕገ መንግሥቱ መሻሻል ያለበት ሕዝብን ባሳተፈ እና ሕገ መንግሥቱ እራሱ ባስቀመጠው መንገድ ሕግና ሥርዓት በተከተለ አካሄድ ብቻ መሆን አለበት ብሎ ያምናል።
- ፓርቲያችን በፌዴራል ሥርዓቱ በማንኛውም ጊዜ የሚነሡ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች ሕጋዊ፣ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ እንዲሁም የሕዝቦችን አብሮነትና ወንድማማችነት በሚያጠናክር መልኩ እንዲፈቱ ይታገላል፡፡
- የብልጽግና ፓርቲ በዚህ ፕሮግራም የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የመንግሥት ተቋማትን የማስፈጸም ዐቅም ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል፡፡ የፓርቲውን ፕሮግራም ለማሳካት ዕንቅፋት የሚሆኑ፣ የሀገር እና የሕዝብን ጥቅም የሚጎዱ ከኅሊና ቢስነት የሚመነጩ ብልሹ አሠራሮችን፣ ልግመኝነትን እና በተለይም የተደራጀ ሌብነትን በጽኑ ይታገላል፡፡ ፓርያችን የሕግ የበላይነትንና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የተደራጀ ሌብነትን ክምንጩ ለማድረቅ ይሠራል። ሀገራችን ዜጎች ለፍተው በሥራ እና በጥረታቸው ሀብት የሚያፈሩባት እንድትሆን ፓርቲያችን ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ጠንክሮ የሚሠራውን ያህል፣ ሕዝብን እና ሀገርን በሚጎዳ አቋራጭ መንገድ ወይም በሌብነት ሀብት ለማግኘት የሚፈልጉትን ደግሞ በጽናት በመታገል፣ ማኅበረሰባችን የግብረ ገብ ውኃ ልኩን ጠብቆ እንዲጓዝ ይታገላል።
2.3. ዘላቂና አዎንታዊ ሰላምን ማረጋገጥ
- ፓርቲያችን ሀገራችን ህልውናዋ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ትቀጥል ዘንድ ሰላሟ ሊጠበቅላት ይገባል ብሎ ያምናል፡፡ በመሆኑም ማኅበራዊ ሀብቶቻችንን በመጠቀም ሕዝብና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍና በማስተባበር የሰላም ባህል በመገንባት፣ የሕግ የበላይነትን በማስከበርና፣ ፍትሕን በማስፈን እንዲሁም ሀገራዊ መግባባትን በማጎልበት ፓርቲያችን ግጭትን ለማስቆም፣ ዕምቅ ግጭቶችን ለማምከን እና ዘላቂ አዎንታዊ ሰላምን ለማስፈን ይሠራል፡፡
- ፓርቲያችን ከኅብረተሰብ ውስጥ የሚጀምር የሰላም እንቅስቃሴ ከየትኛውም መንግሥታዊ ኃይል በላይ ሀገርን በሰላም የመምራት ታላቅ ጉልበት አለው ብሎ ያምናል። በመሆኑም ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንዲቻል በኅብረተሰቡ ውስጥ የግጭት ቀስቃሽ አስተሳሰቦችና ተግባራትን የሚጠየፍ ሕዝባዊ ባህልን ለማዳበር በተቀናጀ መልኩ ይታገላል።
- ፓርቲያችን ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ግብ ከዴሞክራሲ፣ ከመልካም አስተዳደር እና ከልማት ፕሮግራሞቻችን ጋር በእጅጉ የተቆራኘ እንደሆነ ያምናል፡፡ በመሆኑም አዎንታዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የልማት ሥራዎችና ፍትሐዊነት ማረጋገጥ፣ ያልተማከለና አካታች የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት ብዝኃነትን ማክበር እንዲሁም የጋራ ሕልምና ራዕይ በመፍጠር ለጋራ ዓላማ ስኬት በጋራ መንቀሳቀስ የሚያስችል የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሥራዎችን አቀናጅቶ በመሥራት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ይሠራል፡፡
- የሕግ እና የፍትሕ ተቋማት ምንም እንኳን ተፈጥሯዊ ተግባራቸው የሆነውን ሕግና ሥርዓት ለማስፈን የሚያገለገሉ እንጂ ዜጎችን አፍኖ እና ጨቁኖ ለመግዛትና የገዥዎችን ጥቅምና እና ፍላጎት ለማስጠበቅ እንዳይውል ድርጅታችን ሕግና የፍትሕ ተቋማት መሠረታዊ ዓላማ እና ተግባር የዜጎችን መሠረታዊ ነጻነት፣ መብት፣ እኩልነት በሚያከበር እና የጋራ ጥቅም፣ ማኅበራዊ ፍትሕ፣ ብልጽግና፣ ሰብአዊ ደኅንነትን በሚያረጋገጥ መልኩ ሕግና ሥርዓትን ለማስፈን ፓርቲያችን ይታገላል፡፡ የሕግ ገዥነት መርሖች ማስከበር የሚያስችል እንዲሁም መንግሥት ማኅበራዊ እና ተቋማዊ የሆነ የሕግ ገዥነት ባህል መፍጠር እንዲችል የሚያግዝ ንቁ የሆነ የኅብረተሰብ ተሳትፎ እንዲኖር ይታገላል፡፡
- ዘመናዊና ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በጣምራ በመጠቀም፣ ዕምቅ ግጭትን ማወቅ፤ የቅድመ ዝግጁነትና የምላሽ ዐቅምን በማዳበር ግጭትን ማምከን እና በትምህርትና በሚዲያ የታገዘ የኅብረተሰብ ሰላማዊ ባህል በማዳበር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ፓርቲያችን ይታገላል፡፡